ወጋገን ባንክ “ወጋገን ሞባይል” የተሰኘ የሞባይል መተግበሪያ በይፋ ስራ አስጀመረ

ወጋገን ባንክ “ወጋገን ሞባይል” የተሰኘ የሞባይል መተግበሪያ በይፋ ስራ አስጀመረ

ድሬደዋ የካቲት 14 ቀን 2016 ዓ.ም

ወጋገን ባንክ ወጋገን ሞባይል የተሰኘ የሞባይል ባንክ አገልግሎት መተግበሪያ የድሬደዋ ከተማ ከንቲባ አቶ ከድር ጁሃር በተገኙበት በይፋ ስራ ማስጀመሩን በድሬደዋ ከተማ ባካሄደው ማብሰሪያ ስነስርዓት ላይ አስታወቀ፡፡
በዝግጅቱ ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የድሬደዋ ከተማ ከንቲባ አቶ ከድር ጁሃር ወጋገን ባንክ በአገልግሎቱ ረጅም እድሜ ያስቆጠረ እና ለአገር እድገት አስተዋፅኦ ያበረከተ ባንክ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የወጋገን ባንክ የኢንተርፕራይዝ አገልግሎቶች ም/ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ የኋላሸት ዘውዱ በበኩላቸው ባደረጉት ንግግር ወጋገን ሞባይል መተግበሪያ ፈጣን እና ደህንነቱ የተጠበቀ መሆኑን ገልፀው ደንበኞች ከባንክ ወደ ባንክ ገንዘብ ማስተላለፍ እና የተለያዩ አገልግሎቶች ክፍያ በተሳለጠ ሁኔታ ለመፈፀም ያስችላል ብለዋል፡፡
ደንበኞች የወጋገን ሞባይል መተግበሪያን ከፕሌይ ስቶር ወይም አፕ ስቶር በማውረድ አገልግሎቱን በአምስት ቋንቋዎች ማለትም ፡- በአማርኛ፣ በእንግሊዝኛ፣ ኦሮምኛ፣ትግርኛ እና ሶማልኛ ማግኘት እንደሚችሉ ተጠቅሷል፡፡ በዝግጅቱ ላይ የወጋገን ሞባይል መተግበሪያን አጠቃቀም አስመልክቶ ለታዳሚዎች ገለፃ ተደርጓል፡፡
በተጨማሪም ደንበኞች በማንኛውም ዓይነት ስልክ ወደ *866# በመደወል በአማርኛ እና በእንግሊዝኛ አገልግሎቱን ያለኢንተርኔት መጠቀም የሚችሉ መሆኑ ታውቋል፡፡
በተያያዘም ወጋገን ባንክ ደንበኞች ወደ 866 የነፃ ጥሪ መስመር በመደወል ባንኩ ስለሚሰጣቸው የተለያዩ አገልግሎቶች ድጋፍና መረጃ ማግኘት፣ ቅሬታ እና ጥያቄ ማቅረብ የሚያስችላቸውን የደንበኞች ግንኙነት ማዕከል አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ተገልጿል፡፡ አገልግሎቱ በአምስት ቋንቋዎች ማለትም በአማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ሶማልኛ እና እንግሊዝኛ የሚሰጥ ነው፡፡ወጋገን ባንክ ወደፊትም የደንበኞችን ፍላጎት ያገናዘቡ አዳዲስ የዲጂታል ባንክ አገልግሎቶችን በጥናት ላይ ተመርኩዞ እንደሚያቀርብ አቶ የኋላሸት ገልፀዋል፡፡

ወጋገን ባንክ በዕለቱ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ከመወጣት አንጻር ለሁለት በጎ አድራጎት ድርጅቶች ማለትም ለአሰገደች አስፋው የአረጋውያን መንከባከቢያና ማቋቋሚያ ድርጅት እና ዳዊት ለአረጋውያን በጎ አድራጎት ማህበር በድምሩ ብር 500,000 ድጋፍ አድርጓል፡፡

 

About the Author

Comments are closed.